ከሌሶቶ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ቢዝነስ ልማት ሚኒስቴር የተወጣጡ ልዑካን የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩትን ጐበኙ::
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 13 ቀን 2019 ዓ.ም …ኢሥኢ
ከሌሶቶ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ቢዝነስ ልማት ሚኒስቴር የተወጣጡ ልዑካን በትላንትናው ዕለት በኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ተገኝተው የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
እንግዶቹን የተቀበሉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉጌታ ደርበው እንዳሉት መንግሥት በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ልዩ ትኩረት የጥራት መንደር እንደ አጠቃላይ በተለይም ደግሞ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ መዋዕለነዋይ ፈሶበት መገንባቱን፣ የዘመናዊ መሣሪየዎች ግዢ እንዲሁም ተከላ መፈጸሙንና የባለሙያዎች ሥልጠና የተከናወነና አሁንም በመከናወን ላይ መሆኑን ተናግረው በምንሰጣቸው ሥልጠናዎች መሳተፍ የሚችል አንድ ባለሙያ ከመደባችሁ ያለክፍያ ሥልጠና እንዲወስድ እናደርጋለን በሚል አፍሪካዊ የወንድማማችነት መንፈስ ከመጋበዛቸው በተጨማሪ በሌሎችም አጠቃላይ ጉዳዮች ዙሪያ ተቀራርቦ ለመስራት ያላቸውን ፈቃደኝነት ገልጸው እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።
ከእርሳቸው በማስከተል የኢንስቲትዩቱ የፊዚካል ኬሚስትሪ ሥነ-ልክ ምርምር ተባባሪ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ምስጋናው ፀጋዬ ተቋሙን በተመለከተ አጠቃላይ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ልዑካኑ ላቦራቶሪዎችን ተዘዋውረው እንዲጐበኙም ተደርጓል።
ጐበኚዎቹም በበኩላቸው ለተደረገላቸው ቤተሰባዊ አቀባበል ያላቸውን አክብሮትና ምስጋና አቅርበው በተመለከቱት ነገር መርካታቸውንና አብሮ ለመስራት ያላቸውን ፍላጐትና ተስፋ ገልጸዋል።
ለተጨማሪ መረጃ
Facebook: http://www.facebook.com/emi.ethiopia
Website: www.ethiometrology.gov.et